Tao Te Ching Translation in Amharic - Part 1
Transcribed from Wisdom Ethiopia Amharic Podcast By Bisrat
Please support the creator here: Wisdom Ethiopia YouTube
ምዕራፍ ፩–፳፯ ፩ ሊነገር የሚችል ዳዎ ዘላቂ ዳዎ አይደለም። ሊሰየም የሚችል ስም ዘላቂ ስም አይደለም። ዳዎ የሁለቱም ስም እና ስም አልባ ነው። ስም አልባ — የሰማይ እና የምድር መገኛ ነው። ስም — የእልፍ አእላፍ እናት ነው። ያነሰ ፍላጎት ያለው የህይወትን ሚስጥር ማየት ይችላል። ሁሌ ፍላጊ ግን መገለጫዎቹን ብቻ ይመለከታል። ሚስጥሩም ጥልቅ ነው — ህይወትን የምንረዳበት መንገድ ነው።1 ፪ መላው አለም ውበትን ውብ ሲል ለአስቀያሚነት እውቅና ይሰጣል። መልካሙን ጥሩ ሲል ለክፋት እውቅና ይሰጣል። ስለዚህ መሆን እና ላለመሆን ራሳቸውን ያፈራሉ። አስቸጋሪ እና ቀላል እርስ በርስ ይደጋገፋሉ። ረጅም እና አጭር እርስ በርስ ይነጻጸራሉ። ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ራሳቸውን ይለያያሉ። ዜማ እና ድምጽ እርስ በርስ ይስማማሉ። ፊት እና ኋላ እርስ በርስ ይከታተላሉ። ስለዚህ ጠቢቡ ጉዳዮችን ያለድርግት ያስተዳድራል እና ቃል አልባውን ትምህርት ይለማመዳል። እልፍ አእላፍ ነገሮች ይነሳሉ — ነገር ግን አልጀመራቸውም። እነሱን ወክሎ ይሰራል — ነገር ግን ጥገኛ አያደርጋቸውም። ተግባራቶቹን ይፈጽማል — ነገር ግን ምስጋና አይጠብቅም። እነሱ ላይ ስለማያተኩር ስኬቱ ለዘላለም ይኖራል። ፫ አሸናፊዎችን ባለማወደስ ህዝቡን ከፉክክር እና ከውድድር ማዳን ይቻላል። ለማግኘት አስቸጋሪ የሆኑትን ነገሮች ዋጋ ባለመስጠት የሰዎችን ስግብግብነት መግታት ይቻላል። የሰዎችን ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ባለማሳየት ሀሳባቸውን ሰላማዊ ማድረግ ይቻላል። ስለዚህ ጠቢብ ሆኖ መምራት ማለት — የሰዎችን አእምሮ ባዶ ማድረግ፣ ሆዳቸውን መሙላት፣ ፍላጎታቸውን ማዳከም እና አጥንታቸውን ማጠንከር ማለት ነው። ሁልጊዜም ህዝቡ ምንም አይነት እውቀትም ሆነ ፍላጎት እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። እውቀት ያላቸው ሰዎች እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል። እርምጃ ላለመውሰድ ስትለማመድ ሁሉም ነገር በራሱ ይስተካከላል።2 ፬ ዳዎ ባዶ እቃ ነው — ነገር ግን ሲጠቀሙበት መቼም አይሞላም። ምንጩ የማይታወቅ ቢሆንም የሁሉም ነገሮች አባት ይመስላል። ሹልነቱን ያደበዝዛል። ውስብስብ ነገሮችን ይፈታል። ብርሃኑን ያስተካክላል። አለምን ከሙሉነት ጋር ያገናኛል። በጥልቁ ውስጥ ተደብቋል — ግን ለዘላለም ያለ ይመስላል። የማን እንደሆነ አይታወቅም — ከፍጥረት በፊት የነበረ ይመስላል። ፭ ሰማይ እና ምድር አያዳሉም። እልፍ አእላፍን እንዲያልቅ ተፈልጎ እንደተሰራ ነገር ነው የሚያዩዋቸው። ጠቢቦችም ስሜታዊ አይደሉም። ለይተው የሚወዱት ለይተው የሚጠሉት ነገር የለም። እልፍ አእላፍን እንዲያልቅ ተፈልጎ እንደተሰራ ነገር ነው የሚያዩዋቸው። ሰማይ እና ምድር ልክ እንደ ወናፍ ነው — ባዶ ሲሆን አይዝልም። ሲንቀሳቀስ ደግሞ ብዙ ያመርታል። ብዙ ንግግር ወደ ዝምታ ይመራል። ጸጥታን አጥብቆ መያዝ ይሻላል። ፮ በጭራሽ የማይሞት መንፈስ — ሚስጥራዊቷ እንስት ብለን እንጠራታለን። ምንም እንኳን አጽናፈ ሰማይ ብትሆንም ንጽህናዋ መቼም አትጠፋም። ምንም እንኳን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቅርጾች ብትወስድም እውነተኛ ማንነቷ ሳይበላሽ ይዘልቃል። የሚስጥራዊቷ እንስት መግቢያ በር የፍጥረት መሰረት ነው። ድምጽዋ ስሙ ለፍጥረት አስተጋቡ። ሳይሰለቻት ሁሌ ትገለጣለች። ሳይሰለቻት ወደ ራሷ ትመለሳለች።3 ፯ ሰማይ ዘላለማዊ ነው። ምድርም ዘላቂ ናት። ለምን? ምክንያቱም ለራሳቸው ስለማይኖሩ ነው። ለዛም ነው ዘላለማዊ የሆኑት። ስለዚህ ጠቢብ ሰው ራሱን ከኋላ ያስቀምጣል — ግን ከፊት ይገኛል። ራሱን እንደሌለ ይቆጥራል — ግን አሁንም አለ። የራሱ ጥቅም ስለሌለው ነው የሚፈልገውን ማግኘት የቻለው። ፰ ከፍተኛው የደግነት ደረጃ እንደ ውሀ ነው። ውሀ እልፍ አእላፍ ፍጥረትን ይጠቅማል። ከማንም ጋር ሳይወዳደር ሁሉም ሰው በሚጠላው ቦታ ይፈሳል። ስለዚህ ለዳዎ ቅርብ ነው። ቤት ለመስራት — ቦታ አስፈላጊ ነው። ለአእምሮ ጥራት — ጥልቀት አስፈላጊ ነው። ለአጋርነት — ደግነት አስፈላጊ ነው። ለንግግር — ቃል መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ለማስተዳደር — ስርአት አስፈላጊ ነው። ጉዳዮችን ለማስተናገድ — ብቃት አስፈላጊ ነው። ለማድረግ — ወቅታዊነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ጠብ ከሌለ ጥፋተኛም የለም።4 ፱ ነገሮችን እስካፍንጫ ሳይሞሉ በጊዜ ማቆም የተሻለ ነው። ምንም ቢለዋወን ብንለው መቼም መልሶ መደልደሙ አይቀርም። ምንም ወርቅ እና እንቁ ቤትን ቢሞሉትም ትርፋቸው ደህንነትህን አደጋ ላይ መጣል ነው። በክብር እና በሀብት መመካት የራስን ውድቀት ነው የሚያስከትለው። ስለዚህ የሰማይ መንገድ — ድርጊቱ ሲጠናቀቅ ጡረታ መውጣት ነው። ፲ ነፍስህን እና ስጋህን ሳታስማማ አንዱን ይዘህ ሌላውን መተው ትችላለህ? በጣም አስፈላጊ በሆነው እስትንፋስ ላይ ሙሉ ለሙሉ ትኩረትህን በመስጠት እንደ ጨቅላ መሆን ትችላለህ? የውስጥ እይታህን በማጥራት እይታህን ከመሳሳት መጠበቅ ትችላለህ? ህዝብህን በመውደድ ሀገርህን በማስተዳደር በብልሃት ችግርን መፍታት ትችላለህ? የገነት በሮችን በመክፈት እና በመዝጋት የእናትነትን ሚና ተጫውተሃል? ሁሉንም ነገር ተረድተህ ምንም ጣልቃ ሳትገባ ማስተዋል ትችላለህ? እሱን መውለድ እና ማሳደግ፣ እሱን መፍጠር እና አለመያዝ፣ እሱን ማድረግ እና አለመጠበቅ፣ ማስተዳደር ግን አለመቆጣጠር — ይህ ድብቅ በጎነት ይባላል።5 ፲፩ የጋሪ ጎማ ለመስራት ሰላሳ ሽቦዎች ሰውጠረዋል። ነገር ግን የሰረገላው ጥቅም የተመሰረተው መሀል ባለው ባዶ ቀዳዳ ላይ ነው። ጎማን የሚያጠናክረው በውስጡ ያለው አየር ነው። ስለዚህ ባዶ ቦታ ውስጥ የተሞላው አየር ነው ጠቃሚ ያደረገው። ሸክላ ጀበናም ቢሰራ — ግን በውስጡ ያለው ባዶ ቦታ ነው ጠቃሚ ያደረገው። ቤት ስንሰራ በር እና መስኮትም አብረን እንሰራለን — ግን ክፍሉን ለኑሮ ምቹ ያደረገው ባዶ ቦታው ነው። ስለዚህ የሚጨበጠው ነገር ጠቃሚ ያደረገው የማይዳሰሰው ነው። ፲፪ አምስቱ ቀለሞች አይንን ያውራሉ። አምስቱ ድምጾች ጆሮን ይደፍናሉ። አምስቱ ጣእሞች ምላስን ይጎዳሉ። ስለዚህ ብርቅዬ ነገሮችን ለማግኘት ጉልበትን ማባከን ለጥበብ ጉዞ እንቅፋት ነው። እሽቅድድም እና ውድድር የልብ ስውራት ነው። ስለዚህ ጠቢቡ አለምን ይመለከታል — ነገር ግን ውስጣዊ እይታውን ያምናል። ይህንን አውቆ አንዱን ጥሎ ሌላውን ይወስዳል። ፲፫ ስትሞገስም ስትዋረድም ፍራ። ከፍተኛ ችግር የሚመጣው ራስ ላይ በመጣበቅ ነው። ስትሞገስም ስትዋረድም ፍራ ሲባል ምን ማለት ነው? ሞገስ እንደሰጡህ ሁሉ ስለሚነጥቁ ውርደት ደግሞ ከፍተኛ ችግር ስለሚያመጣ። ከፍተኛ ችግር የሚመጣው ራስ ላይ በመጣበቅ ነው ሲባልስ? ምክንያቱም ራስን እንደ አለም ከፍ አድርጎ መመልከት የጥፋት ምንጭ ስለሆነ። ይህን እይታ ካቆምን ያኔ ምንም አይነት ጥፋት ሊደርስብን አይችልም። ስለዚህ የራስን ጥቅም አስረክብ — ራስን እንደምትወድ ሌሎችን ውደድ — ያኔ ከሰማይ በታች ያለው ሁሉ አደራ ይሰጥሃል። ፲፬ ተመልከት — አይታይም። ከቅርጽ በላይ ነው። ስማ — አይሰማም። ከድምጽ በላይ ነው። ያዝ — አይያዝም። የማይዳሰስ ነው። እነዚህ ሶስቱ ካልተዋሃዱ አይታወቁም። ከላይ ብሩህ አይደለም። ከታች ጨለማ አይደለም። ያልተጠቀሰው ምንነት፣ ቅርጽ አልባው ቅርጽ፣ ምስል አልባው ምስል — ሊገለጥ የማይችል ጥላ ነው። ስታገኘው ፊቱ አይታይም። ስትከተለው ጀርባ የለውም። ስለዚህ የጥንቱን መንገድ አጥብቀህ ያዝ ግን ከጊዜው ጋር ተንቀሳቀስ። የጥንቱን ጅምር ማወቅ የዳዎ መገለጫ ነውና። ፲፭ በጥንት ጊዜ መንገዱን በመለማመድ የተካነ ስውር፣ ሚስጥራዊ እና ጥልቅ ጥበበኛ ነበረ። የሱን ጥልቀት ማወቅ ያዳግታል። ሊታወቅ ስለማይችል ብቻ ነው ለመግለጽ ተገዳጅዬ እንዲህ የምለው — ማያመነታ ነበር — በክረምት ወንዝ እንደሚሻገር ሰው። አንቃቃ ነበር — አደጋ ካላጠቡ አቅጣጫ እንደሚመጣ ስለሚያውቅ። ትሁት ነበር — እንደ እንግዳ። ፈታ ያለ ነበር — ኋላ ላይ እንደሚዛፈፍ ቸልባ። እሱ እውነተኛ ቅርጽ አልባ ነበር — ልክ እንደተራ እንጨት። የተዋሃደ የማይለይ ነበር — ልክ እንደ አፈራማ ውሀ። ባዶ ነበር — ልክ እንደ ዋሻ። አፈራማ ውሀን ወስደህ ካቆየኸው ቀስ በቀስ ግልጽ ይሆናል። እረፍት ላይ ያለ ነገር ቀስ በቀስ ህያው ይሆናል። ዳዎን የሚከተል ጥም ብሎ ከመሙላት ይታቀባል። ስለዚህ መታደስ ሆነ መድከም አይታይበትም። ፲፮ ሙሉ ለሙሉ ውስጣህን ባዶ አድርግ። እርጋታ ይኑርህ። ምንም እንኳን ሁሉም ነገር አንድ ላይ ቢነሳም ሲመለስም ተመልከት። ሁሉም ነገር ያብባል — ግን ውሎ አድሮ ወደ ስሩ ይመለሳል። በእርጋታ እያንዳንዱ እጣፈንታውን ያሟላል። ወደ መሰረቱ ሲመለስ — እርጋታ ይባላል። እርጋታው — ወደ ተፈጥሮ ይመልሳል። ወደ ተፈጥሮ መመለስ — ጽኑነትን ያመጣል። ጽኑነት ሲኖር — ግልጽነት ይመጣል። ግልጽነት — ሁሉንቻይ ያደርጋል። ሁሉንቻይ መሆን — አድልኦን ያስቀራል። የማያዳላ — ንቁ ይሆናል። ንቁ ሰው — የሰማይን መንገድ ይከተላል። የሰማይን መንገድ የሚከተል — ከዳዎ ጋር አንድ ይሆናል። ከዳዎ ጋር አንድ መሆን ስጋዬ ቢሞት የማይነካው ዘላለማዊነትን ይሰጣል። ፲፯ ምርጥ መሪ ሲገዛ መኖሩን እንኳን አይታወቅም። ቀጥሎ የሚወዱት እና የሚያመሰግኑት ይመጣል። ቀጥሎ የሚፈሩት ይመጣል። ቀጥሎ የሚቃወሙት ይመጣል። ካልታመንክ ታማኝ ይጠፋል። ትልቅ መሪዎች ቃላቸውን ተገኝተው ተግባራቸውን ያከናውናሉ ስራቸውን ያጠናቅቃሉ። ሰዎቹ ሁሉ ተፈጥሮን እንደሚከተሉ ይናገራሉ።6 ፲፰ ታላቁ የዳዎ መንገድ ሲረሳ በጎነት እና የስነምግባር ደንቦች አብረው ይነሳሉ። እውቀት እና ብልህነት ሲበዛ ታላቅ ግብዝነት ይከተላል። ቤተሰብ ውስጥ ስምምነት ሲጠፋ ልጆች ፍቅር ይራባሉ። ሀገሪቱ ስትታወክ አስመሳይ አርበኞች ይበዛሉ። ፲፱ ብልህነትን አቁም — እውቀትን አስወግድ — ያኔ ህዝቡ መቶ እጥፍ ይጠቀማል። ጽድቅን ትተህ — አስመሳይነትን ልቀቅ — ያኔ ህዝቡ ወደ ጥልቅ ፍቅር ይመለሳል። ተንኮለኝነትን አቁም — ትርፍን አስወግድ — ያኔ ቀማኞች ይጠፋሉ። እነዚህ ውጫዊ ቅርጾች ብቻ ስለሆኑ በራሳቸው በቂ አይደሉም። ማሳመሪያ ጌጣጌጦች ናቸው። ስለዚህ ግልጽነትን አሳይ፣ ቀላልነትን ያዝ፣ ቅንነትን አብዛ፣ ራስ ወዳድነትን ቀንሱ እና በጥቂቱ ተመኝ። ፳ መማርን አቁም — ጭንቀትህ ያበቃል። አዎ እና አይሆንም መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? በመልካም እና በክፉስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ሌሎች የሚፈሩትን እኔ መፍራት አለብኝ? ብርሃን በየቦታው ስለበራ ጨለማን መፍራት አለብኝ? ሌላው ሁሉ በታላቁ ድግስ እየተደሰተ ነው — የመስዋዕትነትን በሬ እየበላ። እኔ ብቻዬን ያለአቅጣጫ የተንከራተትኩ ነኝ — ገና አፋፍታ እንዳልተማረ ጨቅላ። የሚመለስበት ቤት እንደሌለው ሰው። ሁሉም ሰው ከሚያስፈልገው በላይ አለው። እኔ ብቻ የሆነ ነገር የጎደለኝ ይመስላል። አእምሮዬ የሞኝ ይመስላል — ባልተበረዘ ቀላልነቱ። ሌሎች ነገሮችን ለመስራት ሲጣደፉ እኔ የዚህ አለም እንግዳ ነኝ። የቀረበውን እቀበላለሁ። እኔ ብቻዬን ሞኝ እመስላለሁ። ትንሽ ገብኝ — አገኘው — በቀላሉ ነው የምኖረው። ሌሎች ዝና ለማግኘት ሲጥሩ እኔ ግን ብቻዬን መተውን እመርጣለሁ። ከህዝብ እይታ — ራሴን እቆጥባለሁ። በእርግጥ እኔ ቂል እመስላለሁ — ግን አእምሮዬ ባዶ ነው። በውቅያኖስ ላይ የተንሳፈፍኩ ነኝ። ሁሉም ጓዳቸው ውስጥ ይኖራሉ። እኔ ብቻዬን ውጪ እቆያለሁ። ነገር ግን እኔ ከሌሎች የምለየው — ከታላቁ ዳዎ ሲሳይን መቀበል ስለመረጥኩ ነው። ፳፩ ታላቅ በጎነት ማለት ከዳዎ ጋር መጓዝ ማለት ነው። ዳዎ የማይጨበጥ እና ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ምንም እንኳን የማይታይ ቢሆንም በውስጡም ቅርጾች አሉ። ምንም እንኳን የማይጨበጥ ቢሆንም በውስጡም ነገሮች አሉ። ምንም እንኳን ጥልቅ እና ጨለማ ቢሆንም በውስጡም የህይወት ሀይል አለ። እና ይህ የህይወት ሀይል እጅግ በጣም እውነተኛ ነው — ምክንያቱም በውስጡ የራሱ እውነት ስላለው። ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ስሙ አልጠፋም። የሁሉንም ነገሮች አመጣጥ ማየት ያስችላል። የሁሉንም ነገሮች አመጣጥ በዚህ መንገድ ማየት እንደምችል እንዴት አውቃለሁ? በእሱ አማካኝነት። ፳፪ እጅ ስጥ — እና አሸንፍ። ባዶ ሁን — እና ተሞላ። ታጠፍ — እና ቀጥ ትላለህ። አሮጌ ሁን — እና ትታደሳለህ። ትንሽ ሲኖርህ — እሱ ማግኘት ነው። ብዙ ሲኖርህ ግን — ግራ መጋባት ነው። ስለዚህ ጠቢቡ ይህን አጥብቆ ይይዛል እና ከሰማይ በታች ላለው ሁሉ ምሳሌ ይሆናል። ራሱን አያሳይም — ስለዚህ ይታያል። የራሱን ትክክለኛነት አያጸድቅም — ስለዚህ ታዋቂ ይሆናል። በራሱ አይመካም — ስለዚህ ስራው እውቅና ያገኛል። ስለማይወዳደርም — ማንም ሊወዳደረው አይችልም። የጥንት አባባል "እጅ ስጥ እና አሸንፍ" የሚለው ባዶ ቃል ነውን? በእርግጥም ሙሉነትን የሚያመጣ ነው — የነገሮች ሁሉ መመለሻ ወደ ዳዎ ስለሆነ። ፳፫ ተፈጥሮ ብዙ አትናገርም። ኃይለኛ ንፋስ ሙሉ ቀን አይነፍስም። ኃይለኛ ዝናብ ሙሉ ቀን አይዘንብም። ይህንን የሚያደርገው ማነው? ሰማይ እና ምድር። ሰማይ እና ምድር እንኳን እነዚህን ሙሉ ቀን ማቆየት ካልቻሉ — የሰው ልጅ ምን ያህል ማድረግ ይችላል? ስለዚህ ተግባርህን ከዳዎ ጋር አዋህድ። ከዳዎ ጋር አንድ ከሆንክ — ዳዎ በደስታ ይቀበልሃል። ከመልካም ነገር ጋር አንድ ከሆንክ — ደግነት በደስታ ይቀበልሃል። ከሽንፈት ጋር አንድ ከሆንክ — ሽንፈት በደስታ ይቀበልሃል። በዳዎ የምታምን ከሆነ ዳዎ ያምንሃል። ፳፬ በእግር ጫፉ የቆመ ሰው — አጥብቆ አይቆምም። እግሮቹን አጣምሮ የሚሄድ ሰው — ሩቅ አይሄድም። ራሱን የሚያሳይ ሰው — ብርሃን አይፈነጥቅም። ራሱን የሚያጸድቅ ሰው — እውቅና አያገኝም። በራሱ የሚመካ ሰው — ስራው አይከበርም። የሚኩራራ ሰው — ረጅም ጊዜ አይቆይም። ዳዎ እንደሚለው እነዚህ ነገሮች የተረፉ ምግቦች እና አላስፈላጊ ድርጊቶች ናቸው። ሁሉም ፍጡር ይጠላቸዋል። ስለዚህ የዳዎ ተከታይ አያደርጋቸውም። ፳፭ ከሰማይ እና ከምድር በፊት የተወለደ አንድ ምስቅልቅል ነገር አለ። ዝምተኛ፣ ባዶ፣ ራሱን የቻለ እና የማይለወጥ። በየቦታው የሚንቀሳቀስ እና የማይደክም። የሁሉም ነገሮች እናት ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ስሙን አላውቅም። ዳዎ ብዬ እጠራዋለሁ። በግድ ስም መስጠት ካለብኝ — ታላቅ እለዋለሁ። ታላቅ ማለት ማለፍ ማለት ነው። ማለፍ ማለት መራቅ ማለት ነው። መራቅ ማለት መመለስ ማለት ነው። ስለዚህ ዳዎ ታላቅ ነው። ሰማይ ታላቅ ነው። ምድር ታላቅ ናት። ንጉሱም ታላቅ ነው። በአለም ላይ አራት ታላላቅ ነገሮች አሉ — ንጉሱም ከነዚህ አንዱ ነው። የሰው ልጅ ምድርን ይከተላል። ምድር ሰማይን ትከተላለች። ሰማይ ዳዎን ይከተላል። ዳዎ ደግሞ ተፈጥሮን ይከተላል።7 ፳፮ ክብደት የቀሊልነት መሰረት ነው። እርጋታ የሁከት አለቃ ነው። ስለዚህ ጠቢቡ ቀኑን ሙሉ ቢጓዝም ከባድ ጓዙን አይለይም። ምንም እንኳን ድንቅ እይታዎች ቢኖሩም በሰላም እና በጸጥታ ይቆያል። ታዲያ የሺህ ሰረገላዎች ጌታ ራሱን በአለም ፊት እንዴት አቅልሎ ያሳያል? ቀላልነትን መቀበል — መሰረትን ማጣት ነው። መቸኮል ደግሞ — ራስን ማጣት ነው። ፳፯ ጥሩ ተጓዥ — አሻራ አይተውም። ጥሩ ተናጋሪ — ስህተት አይሰራም። ጥሩ ቆጣሪ — መቁጠሪያ አይጠቀምም። ጥሩ መዝጊያ — ቁልፍ አይፈልግም ግን ሊከፈት አይችልም። ጥሩ ማሰሪያ — ገመድ አይፈልግም ግን ሊፈታ አይችልም። ስለዚህ ጠቢቡ ሁልጊዜ ሰዎችን በማዳን የተካነ ነው — ማንም አይጣልም። እሱ ሁልጊዜ ነገሮችን በማዳን የተካነ ነው — ምንም ነገር አይጣልም። ይህ የተደበቀ ብርሃን ይባላል። ስለዚህ ጥሩ ሰው — የመጥፎ ሰው አስተማሪ ነው። መጥፎ ሰው ደግሞ — የጥሩ ሰው መማሪያ ነው። አስተማሪውን የማያከብር ተማሪውን የማይወድ — ምንም እንኳን ብልህ ቢሆንም በእጅጉ ተሳስቷል። ይህ ትልቅ ሚስጥር ነው።
ማስታወሻዎች
Footnotes
ዳዎ ዴ ቺንግ ምዕራፍ ፩ — የዳዎ ተፈጥሮ ሊነገር እንደማይችል የሚያስረዳው ታዋቂ መክፈቻ። Cf. Laozi, Tao Te Ching, trans. Stephen Mitchell (Harper Perennial, 1988), ch. 1. ↩
ምዕራፍ ፫ — ውዝዋዜ ያለበት ምዕራፍ ሲሆን “ህዝቡን ከእውቀት ማራቅ” የሚለው ሀሳብ በብዙ ተርጓሚዎች ዘንድ እንደ ፖለቲካዊ ሴራ ሳይሆን ከማይጠቅም ኢንቴሌክቹዋል ትዕቢት ማራቅ ተብሎ ይተረጎማል። Cf. D.C. Lau, Lao Tzu: Tao Te Ching (Penguin, 1963), notes to ch. 3. ↩
ምዕራፍ ፮ — “ሚስጥራዊቷ እንስት” (谷神 / 玄牝) በቻይንኛ ፍልስፍና ውስጥ የፈጠራ ምንጭን የሚወክል ተምሳሌት ነው። ↩
ምዕራፍ ፰ — ውሀ ከዳዎ ጋር የሚያመሳስለው ማስመሰል ከዳዎይዝም ማዕከላዊ ምስሎች አንዱ ነው። Cf. Ursula K. Le Guin, Lao Tzu: Tao Te Ching — A Book about the Way and the Power of the Way (Shambhala, 1997), ch. 8. ↩
ምዕራፍ ፲ — “ድብቅ በጎነት” (玄德 xuándé) የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ በምዕራፍ ፲፣ ፶፩ እና ፶፭ ውስጥ ይደጋገማል። ↩
ምዕራፍ ፲፯ — በደረጃ ስለተቀመጡ አራት የአመራር ዓይነቶች የሚያስረዳ ምዕራፍ። ከሁሉ የላቀው ህዝቡ ያሉትን እንደ ተፈጥሯዊ የሚቆጥረው ዓይነት ነው። ↩
ምዕራፍ ፳፭ — “ዳዎ ተፈጥሮን ይከተላል” (道法自然) — ዳዎ ራሱ ከሁሉ በላይ ነው ግን ራሱን ከተፈጥሮ ስርአት ጋር ያስማማል። Cf. Wing-tsit Chan, A Source Book in Chinese Philosophy (Princeton University Press, 1963), p. 153. ↩

